ለሂጅራ ባንክ አ.ማ. ባለአክሲዮኖች በሙሉ

የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ መስፈርት ለማሳወቅ የወጣ ማስታወቂያ

ሂጅራ ባንክ አ.ማ. ታህሳስ 11 ቀን 2018 በአዲስ አበባ ሚሊኒዬም አዳራሽ በሚከናወነው 5ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ በብሔራዊ ባንክ የኩባንያ አስተዳድር መመሪያ ቁጥር SBB 91/2024 በተደነገገው መሰረት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት ምርጫን ያካሂዳል፡፡ ምርጫው በዕለቱ በባለአክሲዮኖች በሚሰየም ጊዜያዊ የቦርድ ጥቆማ እና ምርጫ አስፈጻሚ ኮሚቴ አማካኝነት የሚከናወን ሲሆን

  • 1/3ኛ የቦርድ አባላት ተፅዕኖ ፈጣሪ ባልሆኑ ባለአክሲዮኖች ተጠቁመው በእነዚሁ ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ
  • 1/3ኛ የቦርድ አባላት በሁሉም ባለአክሲዮኖች ተጠቁመው በሁሉም ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ
  • እንዲሁም 1/3ኛ የቦርድ አባላት በነባር ቦርድ ተጠቁመው በሁሉም ባለአክሲዮኖች የሚመረጡ ገለልተኛ ዳይሬክተሮችን (Independent Directors) በመምረጥ የሚከናወን መሆኑን መመሪያው ይደነግጋል፡፡

በመሆኑም በመመሪያው አንቀጽ 9(3) መሠረት የጥቆማና ምርጫ መስፈርት ምርጫው ከሚካሄድበት ቀን አንድ ወር በፊት ለባለአክሲዮኖች መገለጽ ይኖርበታል። በዚህም መሰረት ለዳይሬክተሮች ቦርድ አባልነት ዕጩ ሆነው ለመቅረብ እና ለመመረጥ ከዚህ በታች የተዘረዘሩት መስፈርቶች መሟላት ያለባቸው መሆኑን እያሳወቅን ስብሰባው በሚደረግበት ዕለት መስፈርቱን የሚያሟሉ ዕጩዎችን መጠቆምና መምረጥ የምትችሉ መሆኑን ለመላው የባንካችን ባለአክሲዮኖች እናሳውቃለን፡፡

1) በሁሉም ባለአክሲዮኖች ለሚጠቆሙ እና ለሚመረጡ ዕጩ የቦርድ ዳይሬክተሮች ማሟላት ያለባቸው መስፈርቶች

  1. የቦርድ አባላት ምርጫ ከሚደረግበት ዕለት ሁለት ዓመታት በፊት የባንኩ ባለአክሲዮን የሆነ፣
  2. የቦርድ አባል ሆኖ ለመሥራት ሙሉ ፍቃደኛ የሆነና ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት በቂ ጊዜ ያለው፣
  3. ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ወይም ተመጣጣኝ የትምህርት ደረጃ እውቅና ካለው ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያገኘ፣
  4. በባንኪንግ፣ በፋይናንስ፣ በሪስክ ማኔጅመንት፣ በአካውንቲንግ፣ በማኔጅመንት፣ በኢኮኖሚክስ፣ በሕግ፣ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን፣ በኦዲት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እና በተዛማጅ የሙያ ዘርፍ ቢያንስ 7 (ሰባት) ዓመት የሥራ ልምድ ያለው፣
  5. ከዳይሬክተር የሚፈለጉ ግዴታዎችን ለመወጣት ከጥቅም ግጭቶች ነጻና ገለልተኛ በመሆን ከሌሎች የቦርድ አባላት ጋር በአብሮነት መሥራት የሚችል እና ጥሩ ተግባቦት ያለው፣
  6. ሃቀኛ፣ ታማኝ እና መልካም ስም ያለው፤ በተለይም በማጭበርበር፣ እምነት በማጉደል፣ ትክክለኛ ያልሆነ የሂሳብ መግለጫ በማቅረብና በመሳሰሉት ተከሶ በፍ/ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጥቶበት የማያውቅ፣
  7. በሌላ የፋይናንስ ተቋም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ወይም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይም ሠራተኛ ያልሆነ፤
  8. በራሱ ወይም በሚመራው ወይም ዳይሬክተር በሆነበት ድርጅት ላይ የመክሰር ክስ ያልቀረበበት ወይም የኪሳራ ውሳኔ ያልተሰጠበት፣
  9. ከአራት በላይ በሆኑ ተቋማት ውስጥ በቦርድ ዳይሬክተርነት እየሰራ ያልሆነ፣
  10. በኪሳራ ምክንያት ንብረቱ ለዕዳ ማቻቻያነት ያልዋለበት፣
  11. የባንክ ብድር ባለመክፈሉ ምክንያት ንብረቱ በሐራጅ ያልተሸጠ፣ ተከሶ ያልተፈረደበት ወይም እሱ የሚመራው ወይም ዳይሬክተር የሆነበት ድርጅት ከገንዘብ ተቋማት የተበደረውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ብድሩ ወደ ጤናማ ያልሆነ የብድር ደረጃ ያልዞረበት/ያልገባበት፣
  12. በቂ ስንቅ/ገንዘብ ሳይኖር ቼክ ሰጥቶ ሂሳቡ ያልተዘጋበት፣
  13. ግብር ባለመክፈል ተከሶ ጥፋተኛ ያልተባለ፣
  14. በስብሰባው ዕለት የሚመረጠው ጊዜያዊ የቦርድ አስመራጭ ኮሚቴ አባል ያልሆነ፣
  15. ዕጩ ሆኖ የሚቀርበው እና የሚመረጠው የቦርድ አባል የህግ ሰውነት ያለው ተቋም ከሆነ ተቋሙን በመወከል የቦርድ አባል የሚሆነው ግለሰብ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን መስፈርቶች የሚያሟላ መሆን ይኖርበታል፡፡
  16. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወጡ መመሪያዎች ላይ የተገለጹት ሌሎች መመዘኛዎችን የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡

2) ለገለልተኛ ዕጩ የቦርድ ዳይሬክተሮች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች እና በህግ የተቀመጠውን መስፈርቶች የሚያሟሉ ገለልተኛ ዕጩ ዳይሬክተሮች በዳይሬክተሮች ቦርድ ተመልምለው ለጊዜያዊ አስመራጭ ኮሚቴው በዕጩነት በማቅረብ በኮሚቴው አማካኝነት ለምርጫ ይቀርባሉ፡፡

ማሳሰቢያ

  • የገለልተኛ ቦርድ አባላት (Independent Directors) ዕጩዎች ጥቆማን ሳይጨምር የሁሉም ቦርድ አባላት ጥቆማና ምርጫ የሚካሄደው በመደበኛ ጠቅላላ ጉባኤው ዕለት ነው፡፡
  • ባንካችን ተጽዕኖ ፈጣሪ ባለአክሲዮኖች የሌሉት በመሆኑ ሁሉም የቦርድ አባላት በመመሪያው አንቀጽ 9.12 መሰረት በሁሉም ባለአክሲዮኖች ይመረጣሉ።
  • አጠቃላይ የቦርድ አባላት ቁጥር 13 ሲሆን፤ በገለልተኛ የቦርድ አባልነት 4 እንዲሁም ገለልተኛ ባልሆኑ የቦርድ አባልነት 9 ዳይሬክተሮች ይመረጣሉ።
  • የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት በቦርድ አባልነት መመረጥ አይችሉም፡፡
  • አንድ ባለአክሲዮን ራሱን በእጩነት መጠቆም ይችላል፡፡
  • አሁን ያሉ ዳይሬክተሮች መመሪያው በሚፈቅደው መሠረት በድጋሚ ሊመረጡ ይችላሉ።
  • ከአጠቃላይ የቦርድ አባላት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ሴቶች በቦርድ አባልነት መመረጥ አለባቸው፡፡
  • ከማህበሩ ፀሐፊ ውጭ ሁለት የባንኩ ሠራተኞች የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው ሊመረጡ ይችላሉ።
  • የባንኩ የቦርድና የማኔጅመንት አባላት እንዲሁም የባንኩ ሠራተኞች ባለአክሲዮኖችን ወክለው ድምፅ መስጠት አይችሉም።

የማህበሩ ፀሐፊ ሂጅራ ባንክ አ.ማ.

Leave A Comment